Jeremiah 44

ጣዖትን ማምለክ ያስከተለው ጥፋት

1በግብፅ ሰሜናዊ ክፍል በሚግዶል፣ በጣፍናስና በሜምፎስ
ዕብራይስጡ ኖፍ ይላል።
እንዲሁም በግብፅ ደቡባዊ ክፍል
ዕብራይስጡ ከጳትሮስ ይላል።
ስለሚኖሩት የአይሁድ ሕዝብ እንዲህ የሚል ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ፤
2“የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ላይ ያመጣሁትን ታላቅ ጥፋት አይታችኋል፤ ዛሬ ማንም የማይኖርባቸው ባድማ ሆነው ይታያሉ፤ 3ይህም የሆነው ስላደረጉት ክፋት ነው። እነርሱም ሆኑ እናንተ ወይም አባቶቻችሁ ላላወቋቸው ለሌሎች አማልክት በማጠንና በማምለክ አስቈጥተውኛል። 4እኔም፣ ‘ይህን የምጠላውን አስጸያፊ ነገር አታድርጉ’ በማለት አገልጋዮቼን ነቢያትን ደጋግሜ ላክሁባቸው። 5እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ልብም አላሉም፤ ከክፋታቸው አልተመለሱም፤ ለሌሎችም አማልክት ማጠን አልተውም። 6ስለዚህ መዓቴና ቍጣዬ ፈሰሰ፤ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ላይ ነደደ፤ ዛሬ እንደሚታዩትም ማንም የማይኖርባቸው ፍርስራሾች አደረጋቸው።

7“አሁንም የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ዘር እንዳይቀርላችሁ ወንዶችና ሴቶች፣ ልጆችና ሕፃናት በይሁዳ እንዳይገኙ ለምን እንዲህ ዐይነት ታላቅ ጥፋት በራሳችሁ ላይ ታመጣላችሁ? 8ልትኖሩባት በመጣችሁባት በግብፅ ምድር ለሌሎች አማልክት በማጠን፣ እጆቻችሁ ባበጇቸው ነገሮች ለምን ታስቈጡኛላችሁ? በምድር ባሉት ሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የርግማንና የመዘባበቻ ምልክት ለመሆን ራሳችሁን ታጠፋላችሁን? 9በይሁዳ ምድርና በኢየሩሳሌም መንገዶች አባቶቻችሁ የይሁዳ ነገሥታትና ሚስቶቻቸው፣ እንዲሁም እናንተና ሚስቶቻችሁ ያደረጋችሁትን ክፋት ረስታችሁታልን? 10እስከ ዛሬ ድረስ ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ ክብርን አልሰጡኝም፤ በእናንተና በአባቶቻችሁ ፊት ያኖርሁትንም ሕጌንና ሥርዐቴን አልተከተሉም።’

11“ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በእናንተ ላይ ጥፋት ለማምጣትና ይሁዳን ሁሉ ለመደምሰስ ቈርጬ ተነሥቻለሁ። 12ሄደው በግብፅ ለመቀመጥ የወሰኑትን የይሁዳ ቅሬታዎች ሁሉ እነጥቃለሁ፤ ሁሉም ይጠፋሉ፤ በግብፅ ምድር በሰይፍ ይወድቃሉ፤ በራብ ያልቃሉ፤ ከትንሽ እስከ ትልቅ በሰይፍና በራብ ይሞታሉ፤ የመነቀፊያና የድንጋጤ፣ የመረገሚያና የመዘባበቻ ምልክት ይሆናሉ። 13ኢየሩሳሌምን እንደ ቀጣሁ፣ በግብፅ የሚኖሩትን በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር እቀጣለሁ፤ 14ወደ ግብፅ የመጡት የይሁዳ ቅሬታዎች ወደ ይሁዳ ለመመለስ ቢመኙም ከጥቂት ስደተኞች በስተቀር አምልጦ ወይም ተርፎ ወደ ይሁዳ የሚመለስ አንድም ሰው አይኖርም።’ ”

15ሚስቶቻቸው ለሌሎች አማልክት ማጠናቸውን ያወቁ ወንዶች ሁሉና በዚያ የነበሩት ሴቶች ሁሉ ይህም ማለት በሰሜንና በደቡብ ግብፅ
ዕብራይስጡ በግብፅና በጳጥሮስ ይላል።
የሚኖረው ሕዝብ ሁሉ ታላቅ ጉባኤ ሆነው ለኤርምያስ እንዲህ አሉት፤
16“አንተ በእግዚአብሔር ስም የነገርኸንን መልእክት አንሰማም፤ 17እናደርጋለን ያልነውን ሁሉ እናደርጋለን፤ አባቶቻችን፣ ነገሥታታችንና ባለ ሥልጣኖቻችን በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች እንዳደረጉት ሁሉ እኛም ለሰማይዋ ንግሥት እናጥናለን፤ የመጠጥ ቍርባን እናፈስስላታለን። በዚያን ጊዜ የተትረፈረፈ ምግብ ነበረን፤ በመልካም ሁኔታ እንገኝ ነበር እንጂ ምንም ክፉ ነገር አልገጠመንም። 18ነገር ግን ለሰማይዋ ንግሥት ማጠንና የመጠጥ ቍርባን ማፍሰስ ከተውን ወዲህ ሁሉን ነገር ዐጥተናል፤ በሰይፍና በራብም እያለቅን ነው።”

19ሴቶቹም፣ “ለሰማይዋ ንግሥት በምናጥንበትና የመጠጥ ቍርባን በምናፈስስበት ጊዜ፣ በምስሏ ዕንጐቻ ስንጋግርና የመጠጥ ቍርባን ስናፈስስላት ባሎቻችን አያውቁም ነበርን?” አሉ።

20ኤርምያስ ይህን መልስ ለሰጠው ሕዝብ፣ ለወንዶችና ለሴቶች ሁሉ እንዲህ አለ፤ 21“እናንተና አባቶቻችሁ፣ ነገሥታታችሁና ባለሥልጣኖቻችሁ እንዲሁም የምድሪቱ ሕዝብ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ያጠናችሁትን እግዚአብሔር የማያስታውሰውና የዘነጋው ይመስላችኋልን? 22እግዚአብሔር ክፉ አድራጎታችሁንና አስጸያፊ ተግባራችሁን ሊታገሥ ባለመቻሉ፣ ዛሬ እንደ ሆነው ምድራችሁ የርግማን ምልክትና ሰው የማይኖርበት ባዶ ምድረ በዳ ሆኗል። 23ዕጣን በማጠን በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአት ስለ ሠራችሁና ቃሉን ስላልጠበቃችሁ ሕጉን፣ ሥርዐቱንና ትእዛዙን ስላላከበራችሁ ዛሬ እንደምታዩት ጥፋት መጥቶባችኋል።”

24ኤርምያስም ለሕዝቡና ለሴቶቹ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “በግብፅ የምትኖሩ የይሁዳ ሕዝብ ሁሉ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 25የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እናንተና ሚስቶቻችሁ፣ “ለሰማይዋ ንግሥት ለማጠንና የመጠጥ ቍርባን ለማፍሰስ የተሳልነውን ስእለታችንን በርግጥ እንፈጽማለን” ብላችሁ የገባችሁትን ቃል በተግባር አሳይታችኋል።’

“እንግዲያውስ ወደ ኋላ አትበሉ፤ ቃል የገባችሁትን፣ ስእለታችሁንም ፈጽሙ።
26በግብፅ የምትኖሩ አይሁድ ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘ከእንግዲህ ወዲህ በየትኛውም የግብፅ ክፍል የሚኖር ማንኛውም አይሁዳዊ፣ “ሕያው እግዚአብሔርን!” ብሎ ስሜን እንዳይጠራ፣ እንዳይምልም በታላቁ ስሜ ምያለሁ፤ 27ለመልካም ሳይሆን ለክፉ እተጋባቸዋለሁና፤ በግብፅ የሚኖሩ አይሁድ ፈጽሞ እስኪጠፉ ድረስ በሰይፍና በራብ ይደመሰሳሉ። 28ከሰይፍ አምልጠው፣ ከግብፅ ወደ ይሁዳ ምድር የሚመለሱት በጣም ጥቂት ሰዎች ይሆናሉ። በግብፅ ምድር ለመኖር የመጡት የይሁዳ ቅሬታ ሁሉ፣ ከእኔ ወይም ከእነርሱ የማንኛችን ቃል እንደሚጸና ያውቃሉ።

29“ ‘በእናንተ ላይ አመጣለሁ ያልሁትን ክፉ ነገር እንደሚፈጸም ታውቁ ዘንድ በዚህ ስፍራ እንደምቀጣችሁ ይህ ምልክት ይሁናችሁ’ ይላል እግዚአብሔር 30እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ ‘የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን ሊገድለው ለፈለገው ጠላቱ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር አሳልፌ እንደ ሰጠሁ፣ እንዲሁ የግብፅን ንጉሥ ፈርዖን ሖፍራን ሊገድሉት ለሚፈልጉ ጠላቶቹ አሳልፌ እሰጠዋለሁ።’ ”

Copyright information for AmhNASV